የቱሪስት መስህቡ አይነት፡ : ሐይማኖታዊ
የቱሪስት መስህቡ ያለበት ቦታ፡: በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ ፉቻሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር
የሀድር ሼህ መስጅድ በወረዳችን ከሚገኙ ምርጥ የቱሪስት መስህቦች አንዱ ነው፡፡ ይህ መስጅድ የሚገኘው በፉቻሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን ከወረዳው ዋና ከተማ በሰሜን ምስራቅ ዋናውን መንገድ ይዞ በቅርብ ርቀት ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው መስጅድ የተመሰረተው በሀድር ሼህ (ሼህ ስራጅ አህመድ ረህሜ) ናቸው፡፡ ይህም የተሰራው በአፄ ምንሊክ ዘመን ነበር፡፡ ይሁንና ባልታወቀ ሁኔታ መስጅዱ ሁለት ጊዜ ተቃጥሎዋል፡፡ በምትኩም አሁን የሚገኘውን መስጅድ ጣሊያን ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ማለትም በ1920 አካባቢ ተሰርቷል፡፡ መስጅዱም የተሰራው ሙሉ በሙሉ ከፅድ እንጨት ነው፡፡ እንጨቱም የመጣው ሙህር ከሚባል ቦታ ነው፡፡ የተሰበሰበውም በህዝቡ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሀገሩን ለማረጋጋት በሚል የቀጥበሬ ሼህ በመጡበት መስጅዱ አካባቢ እንደሚሆናቸውና የዋልይ ቦታ መሆኑን ነግሯቸው ወደ መስጅዱ መጥተው ሰፈሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከቀጥበሬ ሼህ የጠበቀ ግንኙነት ተፈጠረ፡፡ በእድሜ ግን የሀድር ሼህ ይበልጣሉ፡፡ መሪነቱን ግን የቀጥበሬ ሼህ ነበር የያዙት ምክንያቱም የቀጥበሬ ሼህ በዚያን ጊዜ በብዙ ቦታ የሚታወቁና ዝነኛም ስለነበሩ ነው፡፡ የሀድር ሼህ የተወለዱት በአሁኗ ውሾ አላሳዩ በሚል ልዩ መንደር ነው፡፡ ይሁንና ለዲናቸው በነበራቸው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳና በውሪሮ ህዝብ የጠነከረ ፍላጎት የተነሳ ከውሾ ወደ ኤራጎፋን መንደር መጡ፡፡ ኤራጎፋን በፉቻሬ ቀበሌ የሚገኝ መንደር ነው፡፡ ሼሁም ሲመጡ በአካባቢው ህ/ሰብ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተሰሚነት አገኙ፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስልምናን ዲን በከፍተኛ ደረጃ ማስተማራቸውን ቀጠሉ፡፡ እስካሁንም ድረስ በእጅ የተፃፉት ክታቦች ለዚሁ ስራቸው ህያው ምስካሬ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ክታቡንም ለመፃፍ የተጠቀሙት ዘዴ ሼኩን ከፍተኛ ችሎታ እንደነበራቸው ያስገነዝባል፡፡ በዚያን ወቅት ለቀለምነት የተጠቀሙባቸው ነገሮችን ብንወስድ ኢኒሞ (ከቀርከሀ ሽፋን የሚሰራ ቀለም)፣ሩማን የሚባል ፍሬ በመጭመቅ ሲሆን ፤ለመፃፊያነትም እንጨት ተጠቅመዋል፡፡ ቀለሞችም በቀላሉ እንዳይሸሩና እንዳይለቁ በማሰብ የሙጫ (አንጨቆ) መጠበቂያ ተጠቅመዋል፡፡ ምን ይህ ብቻ የሀድር ሼህ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊም ጭምር ታታሪና ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ትልቅ ዑለማ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ በአካባቢ ለሚኖሩት ህ/ሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የእንሰትና የቀርከሀ ተክሎችን እንዲያረባ ያደረጉ ትልቅ ጀግና ናቸው፡፡ የሀድር ሼህ አብዛኛውን ጊዜ ህ/ሰቡን ከልመና ራሱን እንዲያርቅና ጠንክሮ ራሱን ሰው እንዲያደርግ ያበረታቱ ነበር፡፡ ልመናንም አምርረው ይጠሉ ነበር፡፡ ሀድር ሼህ አብዛኛውን ጊዜ ረፊቆቻቸው /ጓደኞቻቸውን/ የሚያስተናግዱበት ሀለዋ የሚባል ቦታ ሰርተው ይጠቀሙ ነበር፡፡ የሀድር ሼህን ስራ በዚች አጭር ፅሑፍ ጨርሶ ለመጥቀስ ባይቻልም ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ የሀድር ሼህ አላህ ይዘንላቸውና በ1962 እንደ ኢትዮጵያን አቆጣጠር ከዚች አለም በሞት ተለዩ፡፡ ከዚያም በኃላ የተኳቸው ልጆቻቸው ሼህ ኑር ሁሴን ናቸው፡፡ ሼህ ኑርሴንም የአባታቸውና ፈለግ በመከተል አባታቸው የሚያከናውናቸውን ስራ በብቃት ተወጥተውታል፡፡ በወረዳው ከሚገኙ ዑለማዎች በመሆን ህ/ሰቡ እምነቱንና ደህንነቱን ጠብቆ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክተዋል፡፡ ይሁንና የማይሞት የለምና እነሱም በ1993 እንደ ኢዮጵያን አቆጣጠር ከዚች አለም በሞት ተለዩ፡፡ አላህ ይዘንላቸው፡፡ ከሁሉም ግን የነኚህን ታሪክ እንዲዘከር ካደረጉት መካከል ያለምንም ውሃ ልክ የተሰራው መስጅድ እስካሁንም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ የሚገኝ አስገራሚ መስህብ ነው፡፡ በአሁኑም ወቅት መስጅዱ ስሙን ይዞ እንዲቆይ የሼህ ኑር ሁሴን ልጅ ሰይድ አብደላ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም የአካባቢ ህ/ሰብና አፍቃሪያቸው በሙሉ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በመስጅዱም ከድሮ ጀምሮ የሚከበር የመውሊድ በዓል በከፍተኛ ደረጃ ይከበራል፡፡
© 2026/27 G.C የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ፔጅ . All Rights Reserved
By logging in you agree to our Terms and Conditions and Privacy Policy