በዝርዝር

አጃሞቴ መኩላ (ሶርጋን መስጊድ)

የቱሪስት መስህቡ አይነት፡ : ሐይማኖታዊ

የቱሪስት መስህቡ ያለበት ቦታ፡: በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ ውሾ ቀበሌ

በዝርዝር

አልቾ ውሪሮ ወረዳ ጥንታዊና ታሪካዊ መስህቦች ከሚገኙባቸው ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ የቀደምት የሰው ልጅ አጠቃላይ አኗኗር የሚያስነብብ ታሪካዊ የሆነውን ሶርጋን መስጅድ ልናሳውቃችሁ ወደድን፡፡ ይህ መስጅድ የሚገኘው በውሾ ቀበሌ ከወረዳው ዋና ከተማ ቃዋቆቶ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ዳገት ጥግ ይገኛል፡፡ ታሪካዊነቱ ደግሞ በጥንት ጊዜ ማለትም ከዛሬ 450 ዓመት በፊት ከምስራቅ የሀገራችን ክፍል ወይም ከደቡብ አረቢያ ከመጡት ግለሰቦች መካከል አምስቱ የሥልጤ ብሔረሰብ ቀደምት ሴት አያቶች ወደ ወረዳችን መጥተው በመስፈር ለወረዳዋ ዋና ከተማ ስያሜ መንስኤ እንደሆነ ታሪክ ያወሳል፡፡ ከእነዚህም አንዷ የሆነችው ጊስቲ ሙሉካ (አጃሞት መኩላ) ይህች ሴት አምስቱ ወደ ተለያዩ ቦታ ሲለያዩ እሷ የሄደችው ሶርጋን ሚባልበት ቦታ ነበር፡፡ በሄደችበትም ቦታ መስጅዱ እንዳሰራች በታሪክ ይናገራል፡፡ መስጅዱ ያረፈበትንም ቦታ በምናይበት ወቅት ያኔ ማለትም በዛ ዘመን የነበሩ ማህበራዊ ሁኔታዎችን መገመት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱም እዛ ቦታ ላይ ሆኖ በርካታ አካባቢዎችን በግልፅ መቃኘት ይቻላል፡፡ እንዲሁም በውስጡ በዋነኛነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል በእጅ የተፃፈ የተለያዩ ጽሑፎች በቅርስነት ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መስጂድ የሚከፈተው በየሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነው፡፡ ቀናቶቹም ሐሙስና ሰኞ ናቸው፡፡ በተለይም ሐሙስ በየሳምንቱ ከተለያዩ አካባቢ በሚመጡ ሰዎች ሳምንታዊ ዱአ ይደረግበታል፡፡ ከነዚህ ሁለት ቀናቶች ውጪ ግን መክፈት ብዙም ተቀባይነት የለውም፡፡ ሌላው ደግሞ ስለ ትልቁ መስጂድ መረጃዎችን ፈልገን ከአካባቢው የታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎች እንዳወሱን እነሱ ካወቁበት ጊዜ በፊት አሁን ካለው ከትልቁ መስጂድ ሶስት ረጃጅም ዕድሜ ያላቸው መስጅዶች አርጅተው እንደፈረሱ ነው፡፡ አሁን ያለው መስጅድ ከ35 ዓመት ያላነሰ ዕድሜ እንዳስቆጠረ ይነገራል፡፡ ከላይ ከነገርናችሁ በተጨማሪ ዋነኛው ሚታወቅበት በየዓመቱ ማለትም የካቲት ወር የሚካሄደው ታላቁ የመውሊድ በዓል የሚከበርበት መሆኑ ነው፡፡ ሌላ በዓል አዲስ አባባን ጨምሮ በተለያዩ ኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ የስልጤ፣ የጉራጌ እንዲሁም የሌላም ብሔር ተወላጆች ያችን ቀን ናፍቀውና ጠብቀው ወደ ስፍራው መጉረፋቸው የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ ይህም በመሆኑ ስፍራው ለምቶ የበለጠ ሳቢና ማራኪ የቱሪስት መስህብ ሆኖ የወረዳችን መልካም ገፅታ ለመገንባት ሂደት የሚጫወተው ሚና በጣም ከፍተኛ መሆኑና በቀጣይ ስፍራው ተጠንቶ ቀደምት የነበረው የብሔረሰቡን ጥንት ባህልና ታሪክ እሴቶች ታውቀው እንዲከበሩና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅና ለማልማቱ የላቀ ተሳትፎ በማድረግ ቱሪዝም ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከግብ እንዲደርስ ይረዳል በማለት ፅሑፋችንን ቋጨን፡

<

© 2026/27 G.C የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ፔጅ . All Rights Reserved